የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የስልጠናና የልምድ ልውውጥ መርሀ- ግብር አካሄደ
የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የስልጠናና የልምድ ልውውጥ መርሀ- ግብር አካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርማቲክስ ኮለጅ ስለ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር አጻጻፍ፣ ስልቶች፣ መመዘኛዎችና ስለሚገኙ ስኬቶች የሚመለከት ሀገራዊ የስልጠናና የልምድ ልውውጥ መርሀ-ግብር ግንቦት 16/2017 ዓ.ም በአዲሱ የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ወርቁ አበበ፣ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ መምህራንና ተመራማሪዎች በመርሀ -ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የሚሰሩ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምሮች በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ እንዲሆኑ ማስቻል እና ወጣት ተመራማሪዎች ልምድ ካላቸው አንጋፋ ተመራማሪዎች እውቀትና ልምድ እንዲወስዱ ማስቻል ከስልጣናው ዓለማዎች መካከል በዋናነት እንደሚጠቀሱ ዶ/ር ወርቁ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡
የሰው ልጅን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ የማህበራዊ መስተጋብርና የአስተዳደር ስርዓትን እየቀየረ ስለመጣው " ኢንፎርሜሽንና የዲጂታል ቴክኖሎጂን" በተመለከተ ስልጠና በመዘጋጀቱ ደስታቸውን በመክፈቻ ንግግራቸው የገለጹት ዶ/ር ካሳሁን፣ ወጣት መምህራንና ተመራማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ከሚሰጠው ስልጠና በተጨማሪ ከአንጋፋ ተመራማሪዎች የህይወት ተሞክሮ ትምህርት መውሰድ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
ከሰዓት በፊት በነበረው በዕለቱ መርሀ-ግብር በቴክኖሎጂው ዘርፍ በሀገር ውስጥና በሀገር ውጭ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱት ምሁር በዶ/ር ጥበበ በሻህ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር አጻጻፍ፣ ስልቶች፣ መመዘኛዎችና ስኬቶች በተመለከተ በገለጻ ቀርቧል፡፡ ከሰዓት በኋላ በተካሄደው የ “ቡና ወግ” በተሰኘው መርሀ- ግብር በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በሀገር ውስጥና በሀገር ውጪ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱት ምሁር ፕ/ር ቡሻ ተአ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ስልጠናውን የሰጡት ዶ/ር ጥበበ በየተሰማሩበት የትምህርትና የሙያ ዘርፍ እንዴት ውጤታማ ሊሆኑ እንደቻሉ ለተሳታፊዎች በሚማርክ አገላለጽ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
የዕለቱን ስልጠናና የተደረገውን የልምድ ልውውጥ ከተካፈሉ ወጣት ተመራማሪዎች መካከል እጩ ዶ/ር ገ/ሚካኤል ክብረትና የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዋ ሄለን ትዛዙ ይገኙበታል፡፡ ተመራማሪዎቹ ከፕሮግራሙ በርካታ እውቀትና ትምህርት አዘል ቁም ነገሮችን እንዳገኙበት በደስታ ስሜታቸውን አጋርተውናል፡፡
**************************************
ለልህቀት እንተጋለን!
የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ግንቦት 16/2017 ዓ.ም
What's Your Reaction?