በጎንደር የኒቨርሲቲ ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ አዘጋጅነት ሰው ሰራሽ አስታውሎት በትምህርት ላይ ያለው ሚና (AI for Education) በሚል ዓብይ ርዕሰ ጉዳይ ከጥር 19/2018 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ተግባራዊ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ይህን ስልጠና ለመስጠትና ልምዳቸውን ለማካፈል ከሀገረ አሜሪካ የመጡት ፕ/ር ነጋ ወርቁ ሲሆኑ፣ ፕ/ሩ በሰው ሰራሽ አስታውሎትና በሌሎች የትምህርትና የሙያ መስኮች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያካበቱ ምሁር መሆናቸውን ከግለ-ታሪካቸው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካይና የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የዩኒቨርሲቲው የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ወርቁ አበበ፣ ከተለያዩ ኮሌጆች የመጡ ዲኖችና መምህራን፣ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስልጠናው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ባህር አቋርጠው በሰው ሰራሽ አስታውሎት ዙሪያ ያላቸውን ልምድና እውቀት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለማካፈል ፈቃደኛ ሆነው ለመጡት ለ ፕ/ር ነጋ ወርቁ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ምስጋና ያቀረቡት የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ወርቁ ናቸው፡፡
ሰው ሰራሽ አስታውሎትን ለመማር ማስተማሩ አወንታዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ዋነኛ ዓለማ ያደረገውን ተግባራዊ ስልጠና ለመካፈል ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ኮሌጆች የተሰባሰቡትን ተሳታፊዎች በማመስገን መርሀ-ግብሩን ያስጀመሩት ዶ/ር ካሳሁን፣ ሰልጣኞች ስልጠናውን በንቃት በመሳተፍ፣ በዘመኑ ተጽዕኖ እየፈጠረ የሚገኘውን የዕለቱ ዓብይ ጉዳይ በተመከተ በርካታ ተሞክሮዎችንና ቁም ነገሮችን በመቅሰም እራሳቸውን፣ ማህበረሰባቸውን ብሎም ሀገራቸውን በሚጠቅም መልኩ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን እንዲገለገሉበት አሳስበዋል፡፡
በመርሀ-ግብሩ መሰረት ፕ/ር ነጋ ሰው ሰራሽ አስታውሎትን እንዴት ለመማር ማስተማሩ ሂደት በበጎ መልኩ መጠቀም እንደሚቻል የግላቸውንና የውጪ ሀገር ተሞክሯቸውን በማጣቀስ ለተሳታፊዎች በገለጻ እያብራሩና በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ የፕሮፌሰሩን ገለጻ መነሻ በማድረግ በየመሀሉ ላይ ከተሳታፊዎች ጋር የገጽ ለገጽ ውይይትና የልምድ ልውውጥ እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ በውይይቱም ስለ ሰው ሰራሽ አስታውሎት አወንታዊና አሉታዊ ጎኖች እየተነሱ ይገኛሉ፡፡ የስልጠናውን ዓብይ ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ በተሳታፊዎች ለተነሱ አሉታዊ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በአሰልጣኙ በኩል ምክረ ሀሳብና ምላሽ እየተሰጠባቸው ይገኛል፡፡
ይህ ተግባራዊ ስልጠና ዛሬ ጥር 20/2018 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በዶ/ር ካሳሁን የመዝጊያ ንግግር ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
***************
ጥር 20/2018ዓ.ም