የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች የመመረቂያ ፕሮጀክቶቻቸውን ለውድድር አቀረቡ

የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች የመመረቂያ ፕሮጀክቶቻቸውን ለውድድር አቀረቡ

የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች የመመረቂያ ፕሮጀክቶቻቸውን ለውድድር አቀረቡ

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች በተለያዩ መስፈርቶች በየትምህርት ክፍሉ ተገምግመው የተመረጡ አራት ፕሮጀክቶች ግንቦት 22/2017 ዓ.ም. ለፍጻሜ ውድድር ቀርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው አዲሱ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የተካሄደውን ይህን የፍጻሜ ውድድር ነርቸር የተሰኘ ፕሮጀክት ስፖንሰር ያደረገው ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ የዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዚዳንቶች፣ የነርቸር ፕሮጀክት ዋና ዳይሬክተር ፕ/ር ቢኒያም ጫቅሉ፣ የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ወርቁ አበበ፣ የዩኒቨርሲቲው ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መርሀ ግብሩን ታድመዋል፡፡

የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም የማህበረሰባቸውን ችግር በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለመቅረፍ የበኩላቸውን ጥረት በማድረጋቸው የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዘመኑ ፈጣን የቴክኖሎጂ ዘመን እንደመሆኑ መጠን ከኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎች ውጤታማ የሆኑ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች እንደሚጠበቅባቸው በመክፈቻ ንግግራቸው የገለጹት ዶ/ር አስራት፣ ዩኒቨርሲቲው በኮሌጁ ለሚደረጉ ምርምሮች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነቱ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ መርሀ ግብሩን በጋራ ያዘጋጀው የነርቸር ፕሮጀክት ዳይሬክተር ፕ/ር ቢኒያም ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት በበኩላቸው፣ ለሚደረጉ ሳይንሳዊ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችና ምርምሮች ለኮሌጁም ሆነ ለዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅባቸውን እገዛ ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ መርሃ ግብር በተደረገው ውድድር- የኮምፑዩተር ላቦራቶሪ መተግበሪያ ያበለጸጉ የ4ኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪዎች ውድድሩን በአንደኝነት ሲያጠናቅቁ፣ በግብርና ዘመናዊ ግብይት ዙሪያ “እፎይታ” የሚል መተግበሪያ የፈጠሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተማሪዎች ውድድሩን በሁለተኝነት አጠናቀዋል፡፡

ዘመናዊ የውሀ አጠቃቀም መቆጣጠሪያ ሲስተም በመስራት የፈጠራ ስራቸውን ያቀረቡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተማሪዎች ውድድሩን በሦስተኝነት ሲጠናቅቁ የመመረቂያ የማስታወሻ መጽሀፍ መተግበሪያ ያበለጸጉት የኮምቲዩተር ሳይንስ ተማሪዎች በአራተኛ ደረጃ ውድድሩን አጠናቀዋል፡፡

ውድድሩን በ አንደኝነት ላጠናቀቁት እጩ ተመራቂ ተማሪዎች የአስር ሺህ ብር፤ የሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁት ተማሪዎች የሰባት ሺህ ብር ሽልማት የቀረበላቸው ሲሆን ሶስተኛ ሆነው ላጠናቀቁ ዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች የአምስት ሺህ ብር በሽልማት መልክ ነርቸር ከተሰኘው ፕሮጀክት ቀርቦላቸዋል፡፡

በተጨማሪም ለሁሉም አሸናፊዎች የስራ ፈጠራና ሌሎች የስልጠና እድሎች እንደሚመቻችላቸው ከኮሌጁ ዲን ከዶ/ር ወርቁ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

**************************

ለልህቀት እንተጋለን!

የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

ግንቦት 22/2017 ዓ.ም.

 

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow