የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ከሰው ሰራሽ አስታውሎት (AI) እና ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ አራት አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች በ2ኛ ዲግሪ (MSc) መርሀ ግብር ለመክፈት ዓላማ ያደረገ የውስጥ የስርዓተ-ትምህርት ግምገማ ጥር 19/2018 ዓ.ም በአፄ ቴዎድሮስ ግቢ ድህረ-ምረቃ አዳራሽ አካሂዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ወርቁ አበበ፣ ከዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ኮሌጆች የመጡ ዲኖችና የት/ክፍል ኃላፊዎች፣ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሀ- ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ለዘመኑ አስፈላጊ የሆኑ አራት ፕሮግራሞችን ማለትም በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በኮምፒዩተር ትስስርና ደህንነት፣ በድጅታል ግብይትና በዳታ ትንተና እንዲሁም በድጅታል ትራንስፎርሜሽንና ፈጠራ የ2ኛ ዲግሪ መርሀ-ግብር ለመክፈት ታሳቢ ያደረገ የውስጥ ስርዓተ-ትምህርት ግምገማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ኮሌጃቸው ማዘጋጀቱ እንዳስደሰታቸው ዶ/ር ወርቁ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡
መርሀ-ግብሩን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት ዶ/ር ካሳሁን በበኩላቸው፣ ኮሌጁ አስፈላጊውን የፍላጎት ዳሰሳ በማከናወን የዘመኑን ችግሮች በሚያቃልሉ የትምህርት ዘርፎች ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ፕሮግራሞችን ለመክፈት ተገቢውን ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን አያይዘው እንዳሉት ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ ፕሮግራሞችን መክፈት ይበል የሚያሰኝ ቢሆኑም፣ የሚከፈቱት ፕሮግራሞች ግን ተገቢውን የትምህርት ጥራት ስታንዳርድ ሊያሟሉ እንደሚገባ በጽንኦት አሳስበዋል፡፡
******************
ጥር 19/2018 ዓ.ም